በልዑል ዘሩ
በኢትዮጵያ 2008 ዓ.ም ከሰላምና መረጋጋት ይልቅ ነውጥ ጎልቶ ታይቷል ቢባል ያስማማናል፡፡ እንዲያውም በኢሕአዴግ ከ25 ዓመታት የመንግሥትነት ዘመን ፈታኝ የሚባለው ዓመት ይመስላል፡፡ በተለይ ደግሞ ሥርዓቱ አምስተኛውን ዙር ብሔራዊ ምርጫ ‹‹በሙሉ ጠቅላይነት›› አሸንፎ ሥልጣን በጨበጠበት ገና በአንደኛው ዓመት ሰው ሠራሽም ሆኑ የተፈጥሮ እንቅፋቶች አገሪቱን እያንገዳገዱ መሆናቸው ትኩረትን ስቧል፡፡
ዘንድሮ ከመስከረምና ከጥቅምት የፀደይ ወራት አንስቶ በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለዕርዳታ እጁን እንዲዘረጋ አድርጓል፡፡ ይህ በ50 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በስፋትና በቆይታ አስፈሪ የተባለ የተፈጥሮ አደጋ በመንግሥት አቅም ብቻ ቢመከትም፣ አገሪቱን ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ያስወጣ ነው፡፡ በሰው ሕይወት ላይ የሚገለጽ የጎላ ጉዳት ባይከሰትም በእንስሳትና በሰብል ምርታማነት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡
ገዥው ፓርቲ በዚህ ዓመት ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ተፋልመን እናስወግዳለን፤›› ብሎ በሥሩ ያሉ ፓርቲዎች አባላትን ደጋፊዎቹን አንቀሳቅሶና በጉባዔ ወስኖ፣ ጥናት አድርጐ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች (ባለሥልጣናት) ደረጃ የመከረበትን ያህል ሥራው የቀለለው አይመስልም፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ከተሞችና ክልሎች በዝቅተኛ የሥራ ኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሹማምንትን ያባረረው ወይም በሕግ የጠየቀው መንግሥት፣ በላይኛው እርከን የወሰደው እዚህ ግባ የሚባል ዕርምጃ አልታየም፡፡
በዚህ ሒደትም ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ተራራን ለመናድ›› የሚለው መፈክር እንደተንጠለጠለ ይገኛል፡፡ ይህ ነባራዊ ሀቅ ባለበት ሁኔታ ነው ከሞላ ጎደል ለወራት ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ የቀጠለ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (ተቃውሞ) በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው፡፡ በተለይ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በምዕራብ አርሲ፣ ባሌ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋና ምሥራቅ ወለጋ ዞኖች እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ጊዜያት የታየው የሕዝቡ ተቃውሞ አሁንም መፍትሔ ያገኘ አልመሰለም፡፡
በኦሮሚያ ክልል ወጣት፣ አዛውንት፣ የገጠርና የከተማ ሕዝብ ሳይባል በተለይ በኅዳርና በታኅሳስ የነበረውን የተቃውሞ ሠልፍ የተቀላቀሉ ቅሬታ አቅራቢዎች መነሻ ምክንያት ነበረው፡፡ ቢያንስ የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የጋራ ማስተር ፕላንን ትግበራ በመቃወም ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ‹‹ለጊዜውም›› ቢሆን ተስተካከለ ከተባለ በኋላም ግን፣ በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ መልኩን እየቀያየረ እስካሁን ቀጥሏል፡፡ እነ ጀዋር መሐመድን በመሳሰሉ የውጭ ኃይሎች ጥሪ የሚታዘዝም ሆኗል፡፡
በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጐንደር ዞን የተነሳው ‹‹ሰላማዊ›› የሚመስል የሕዝብ ተቃውሞና እንቢተኝነትም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ መነሻው ‹‹የወልቃይት የማንነት ጥያቄ›› ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ መራሹን መንግሥት ፊት ለፊት በመቃወምና በማውገዝ ታጅቦ ቀጥሏል፡፡ ክፉው ነገርም በየአካባቢው በተነሱ ሁከቶችና አለመግባባቶች የሰው ሕይወትና ንብረት ጠፍቶ፣ የአካል መጉደልና የህሊና ቁስለትም ደርሷል፡፡
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቁጥሩ ከ400 ይበልጣል በማለት መከራከሪያ ሲያቀርቡ፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መረጃ መሠረት የቅርብ ጊዜውን ጉዳት ሳይጨምር በኦሮሚያ ክልል ብቻ 173 ዜጐች ሞትና 956 የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ በአማራ ክልልም የ97 ዜጐች ሕይወት ሕልፈትና የ86 ዜጐች የአካል ጉዳት ሲታሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር መዝገብ ላይ የሚያርፍ አጉል ጊዜን አስከትሏል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በጐንደር፣ ባህር ዳር፣ ምሥራቅ ሐረርጌ ሐሮማያ፣ ኮምቦልቻ፣ ጀልዱ፣ ባሌና አርሲ አካባቢዎችና በመሳሰሉት)፣ (ሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ዞን) በተደረገ ሕጋዊም ይበል ሕገወጥ ሠልፍና ሕዝባዊ ቅሬታ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን ጨምሮ የንፁኃን ዜጐች ሕይወትና የአካል ጉዳት አጋጥሟል፡፡
የዘንድሮ ‹‹የተቀናጀ›› የሚመስል ሰላማዊ ብቻ ሳይሆን ኃይል የተቀላቀለበት የሕዝብ ቅሬታ መንግሥትን ክፉኛ ፈትኖታል፡፡ በአንድ በኩል ሠልፈኛው የመንግሥት ተቋማትና የሕዝብ መገልገያዎችን፣ የመንግሥት ‹‹ደጋፊ›› የሚመስሉ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ሀብትና ንብረት ለውድመት ዳርጓል፡፡ ዘረፋ የተፈጸመባቸውም አካባቢዎችም ነበሩ፡፡ በሰሜን ጐንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ የደረሰው ውድመት ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የከፋ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚያሻክሩ፣ 25 ዓመት የተሄደበትን ቋንቋ ተኮር ፌዴራል ሥርዓት ‹‹ፉርሽ›› የሚያስመስሉ ክስተቶችም በገሃድ ታይተዋል፡፡
የተጀመረው ሁከትም ይባል ሕዝባዊ እምቢተኝነት ወደፊት ይቀጥል አይቀጥል ዋስትና ያለ አይመስልም፡፡ በአንድ በኩል በውጭ ካለው ተቃዋሚ አገር ውስጥ እስካለው ድረስ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ የጀመረውን ተቃውሞ ‹‹አጠናክሮ›› እንዲቀጥል ያላሰለሰ ቅስቀሳ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ድረ ገጽ (ትዊተር፣ ፌስቡክ)፣ በውጭ የሚገኙ ሚዲያዎች በተዛባ ታሪክ፣ በአሉባልታና በተፈበረኩ ወሬዎች ጭምር አገሩን ሰንገው ይዘውታል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ሒደቱን ፈጥኖ በውይይት፣ በሰላማዊ ድርድርና በምክክር ከመፍታት ይልቅ ኃይልን አማራጭ ያደረገ መስሏል፡፡ ሕግ ማስከበርና የአገር ደኅንነትን የመጠበቅ ኃላፊነት ቢኖርበትም ይህ ግን በኃይልና መሣሪያ ብቻ ሊመጣ አይችልም፡፡ ይልቁንም ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ሲል የውጭ ኃይሎች ከመጥለፋቸው በፊት ቀድሞ ከሕዝብ ጋር መነጋገር የበለጠ የሚያግባባ መሆኑ ካልታመነበት ችግር አለ ማለት ነው፡፡
እንግዲህ በዚህ ምክንያት ነው ‹‹አገሪቱ ወደ ምስቅልቅል ቀጣና›› እንዳትወድቅ ምን ይደረግ? ከማንስ ምን ይጠበቃል? ወደሚሉ ውይይት ቀስቃሽ ሐሳቦች መግባት የተፈለገው፡፡ ሐሳቡን ደግፈንም ሆነ ተቃውመን ልንነጋገርበት እንደምንችልም እናምናለን፡፡
አሁን ሕዝቡን በጠባብ ምኅዳር መያዝ አይቻልም!
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የተለያዩ ፈታኝ ወቅቶችን ማለፉን በተደጋጋሚ ጊዜያት ተናግሯል፡፡ በደርግ ውድቀት 1983 ዓ.ም.፣ በኤርትራ ጦርነትና በሕወሓት መከፋፈል ወቅት 1993 ዓ.ም፣ እንዲሁም በምርጫ 97 ወቅትና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ሕዝቡን እያወያየ፣ በፀጥታና በደኅንነት ኃይሉ እየታገዘ ችግሮችን ተሸጋግሮ ወደ ሰላማዊ ሁኔታም ተመልሷል፡፡ አሁን ግን ይህን ማድረግ ይቸግረዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ‹‹የአሁኑ አገራዊ ሁኔታ በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ብቸኛ ‹መፍትሔ አምጭነት› ብቻ አይፈታም›› ብለውኛል፡፡ በማስረጃ ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩም፣ በቀዳሚነት የሕዝቡን በየአካባቢው አለመርካት፣ ቅሬታ ማንሳትና ‹‹ይለይለት›› እልህ ውስጥ እየገባ መምጣትን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
ችግሩ በትልልቆቹ (በሕዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት) ክልሎች ብቻ ያለ ይምሰል እንጂ በሐረሪ ክልል፣ በደቡብ (በተለይ በኮንሶና በሸካ) በጋምቤላ ክልል ሄደት መለስ ሲል ታይቷል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በዋና ዋና ከተሞች ከሥራ ማጣት፣ ከድህነትና የኑሮ ውድነት ጋር የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡ በሕገወጥ የመሬት ወረራና መልሶ ማልማት የተፈናቀሉ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ያባዘናቸው፣ ወዘተ ሁሉ ቅሬታ ውስጥ እንደሚሆኑ መገንዘብ አያዳግትም ባይ ናቸው ምሁሩ፡፡ በሌላ በኩል የዴሞክራሲና የነፃነት ዕጦት፣ ከልማቱ ተጠቃሚ አለመሆንና የመገፋት ስሜቶችም መኖራቸውን ያክላሉ፡፡
ሌላኛው ነጥብ በዘንድሮው ወቅታዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ከዓመታት በፊት ጀምሮ በፖለቲካ ልዩነትና በሐሳብ ነፃነት ሰበብ በሕግ የተጠየቁ፣ በፀረ ሽብር ሕጉ የተከሰሱና በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ሁከቶች ‹‹በነውጠኝነት›› የተጠረጠሩ ዜጐች ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡ በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአዲስ አበባና በጋምቤላ አካባቢዎች ቁጥራቸው በርከት እንደሚሉ የሚገመቱ እነዚህ የፖለቲካ ተጠርጣሪዎች ከጀርባቸው የተለያዩ ደጋፊዎችና ቤተሰቦች አሏቸው በማለትም ምሁሩ ይናገራሉ፡፡
ከእነዚህ የአገር ውስጥ የቅሬታ ምንጮች ባሻገር ገዥው ፓርቲ ‹‹ምኅዳሩ ሰፍቷል›› ቢልም በምርጫ 2007 ያረጋገጠው የሥልጣን ጠቅላይነት በመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ላይ እንቅፋት ተደርጎ እየተወሰደ ነው፡፡ በተለይ ከሰላማዊ ተገዳዳሪዎች አለመጠናከርና ‹‹መፈናፈኛ ማጣት›› ጋር ተደምሮ ነፃ ሐሳብ፣ ነፃ ማኅበር፣ መደራጀት፣ ነፃ ፕሬስ… በበቀሉበት ሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ ዕድገት አላሳዩም፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ ከተቃውሞ ሠልፍ በላይ ነፍጥ አንስቶ ለመፋለም የሚሻውን ወገን እያበረከተው እንዳይሄድ ሥጋት አላቸው፡፡
መንግሥት ይህን መሬት ላይ ያለ እውነት ቸል ብሎ ችግሩን በእኔ መዘውር ብቻ እፈታዋለሁ ከሚል ስሌትም መውጣት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ከ25 ዓመታት በኋላ አዲስና ሰፊ የውይይት ምኅዳር መፍጠር የተሻለ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት፡፡
የተቃዋሚ ኃይልና አማራጭ ሐሳብ ስንዘራው በርትቷል
በአገር ውስጥ የሚገኙ ብሔራዊም ሆኑ ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ማኅበሮችና ድርጅቶችን ጨምሮ፣ በውጭ የሚኖሩ ‹‹ጽንፈኛ›› እና ነፍጥ ያነሱ ተቃዋሚዎች አንድ የጋራ ‹‹ጠላት›› አላቸው፡፡ እነዚህ በስትራቴጂ ቢለያዩም በኢሕአዴግ ከሥልጣን መውረድ ላይ የሚስማሙ ኃይሎች እንደ ኤርትራ መንግሥት፣ ግብፅና አንዳንድ የዓረብ መንግሥታትን ድጋፍም አያጡም፡፡ ምዕራቡ ዓለምም ቢሆን ‹‹አርፋችሁ ተቀመጡ›› የሚላቸው እንዳልሆነ ይገመታል፡፡
ሌላው ቀርቶ ካለፉት አራት አሥርት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለፉ፣ በተለያዩ ጊዜያት ከኢሕአዴግ ካምፕ የወጡና የዳር ተመልካች የነበሩ ሁሉ ‹‹የለውጥ›› ሐሳብ ማቀንቀን ይዘዋል፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ማድረግ ካለበት ሥር ነቀል ለውጥ አንስቶ እስከ ሁሉ አቀፍ የፖለቲካ ድርድር እንዲጀመር የመወትወት ብቻ ሳይሆን፣ ሥርዓቱ ይህን ዕድል ካልተጠቀመበትም አገሪቱ አደጋ ላይ እንደምትወድቅ ማሳሰብ ይዘዋል፡፡
በቅርቡ በአሜሪካ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች የጀመሩት ውይይት፣ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ መንግሥት ‹‹ኒዮሊብራል›› የሚላቸው እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ድርጅቶችም የተቃዋሚውን ሐሳብ እየገዙት ይመስላሉ፡፡ (በሰሞኑ የቢቢሲ፣ የአልጄዚራ፣ ሲኤንኤንና ፕሬስ ቲቪ ዘገባዎችና ድርጅቶቹ ያወጧቸው መግለጫ እንደሚያሳዩት)
የእነዚህ ውጫዊ የሚመስሉ ኃይሎች ተፅዕኖ ቀላል ነው እንዳይባል የሚያደርገው ማሳያ ደግሞ፣ ሕዝቡ በተለያዩ ድረ ገጾችና ሚዲያዎች የሚደርሰውን መረጃ ተከትሎ ተቃውሞን እያስቀጠለ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ በተቃውሞ ሠልፍ ስም ሁከት ለመቀስቀስና ከሕግ የሚፃረሩ ተግባራትን ለመፈጸም የሚፈጸመው ድርጊት የአገርንና የሕዝብን ህልውና ክፉኛ የሚደፍቅ ነው፡፡ ቀስ በቀስም የእርስ በርስ ግጭትን የሚጋብዝና አገር የሚያፈርስ እንደመሆኑ ቆም ብሎ ማሰብንም ይጠይቃል፡፡
ገዥው ፓርቲና መንግሥትን ተፅዕኖ ውስጥ ለመክተት ያለመው ‹‹የተቀናጀ›› የሚመስለው ፖለቲካዊ ሁኔታ አደገኛ ጦስንም ሊቀሰቅስ እንደሚችል መታየት አለበት፡፡ አንደኛው የትግራይ ሕዝብ ከጥንት እስከ ዛሬ በአገሪቱ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የነበረውን ድርሻ ቸል በማለት፣ ከሥርዓቱ ጋር እንዲወገዝ የሚደረገው ጥረት ነው፡፡ ይህ የዘረኝነትና የጥላቻ ልክፍት የተጠናወተው አስተሳሰብ ሕዝቡን ‹‹ብቸኛ የሥርዓቱ ተጠቃሚ›› አድርጐ እየሳለው በመሆኑ ሐሳቡን የሚገዛው የለም ሊባል አይችልም፡፡
ሁለተኛው በኦሮሚያ ያለው የተቃውሞ ሠልፈኛ የኦነግን ሰንደቅ ዓላማ አንስቶ በጠባብነት የታወረውን አስተሳሰብ በይፋ ያቀነቅን ይዟል፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ በአሀዳዊነትና በትምክህተኝነት የሚተቸውን ‹‹የቀድሞ ሥርዓቶችን ሰንደቅ›› አንስቶ በየደጃፉ እስከ መስቀል ደፍሯል (በነገራችን ላይ እነዚህ ድርጊቶች በ25 ዓመታት ውስጥ በግላጭ በአገር ውስጥ የተፈጸሙ ኢ ሕገ መንግሥታዊ ሊባሉ የሚችሉ ተግባራት ናቸው)፡፡ እነዚህ ሁለት ጫፍ ላይ ያሉ አስተሳሰቦች ወደ ነፃ ውይይት መጥተው የሐሳብ ፍጭት ካልተደረገባቸውም የተቀበሩ ቦምቦች መሆናቸው አይቀርም፡፡ 25 ዓመታት የተጓዘውን ቋንቋ ተኮር ፌዴራሊዝም ጥያቄ አስነስተውበታል፡፡
ከእነዚህ እውነታዎች አንፃር ሲመዘን መንግሥትና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በአንድ ጊዜም ባይሆን ቀስ በቀስ ወደ ጋራ አጀንዳና ሁሉ አቀፍ ውይይት መምጣት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ሕዝብን ማክበር፣ አገርን መውደድና ነገን ትውልዱ በተስፋ እንዲጠብቀው ማድረግ የሚቻለው በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፡
ቀጣናው ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው
ተደጋግሞ እንደሚባለው አገራችን የምትገኝበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ለቀውስና ትርምስ አመቺ የሚባል ነው፡፡ በአንድ በኩል ከትርምስ ወጥታ በእግሯ መቆም ያልቻለችው ሶማሊያ፣ የውድቀት መንገድን የመረጠችው ደቡብ ሱዳንና ‹‹ሰላም የለም ጦርነት የለም›› ፍጥጫ ውስጥ የከተተችን ኤርትራ ከ68 በመቶ በላይ ድንበራችንን ከበውታል፡፡ ሱዳንና ኬንያም ቢሆኑ ከድንበር፣ ከውኃ አጠቃቀምና ከመሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዘ የውስጥ ጥያቄዎች አሏቸው፡፡
በሌላ በኩል የቀይ ባህር ዙሪያው ፍጥጫ ከመቼውም ጊዜ ከፍ ባለ ደረጃ ለአገራችን ሥጋት እየሆነ መምጣቱን በርካታ ምሁራን እየገለጹ ነው፡፡ የየመን የእርስ በርስ ግጭት፣ የሳዑዲ ‑ ኢራን ፍጥጫ ሳይቀር በኤርትራ መንግሥት ተገለባባጭ ባህሪ ላይ ሲደመር ትኩረትን ሊስብ የሚችል ነው፡፡ በዚሁ መሀል እስራኤልና ቻይና ጭምር ለትልልቆቹ የምፅዋና የአሰብ ወደቦች በመቅረብ በእጅ አዙር ቀጣናዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር እየማሰኑ ይገኛሉ፡፡
በዚህ መዘዝ ይመስላል አንዳንድ ተንታኞች በአሁኑ ወቅት ከኤርትራው አምባገነን ሥርዓት ጋር ጦር መማዘዝ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከሚደርሰው ጫና በላይ፣ በእጅ አዙር ሻዕቢያን የሚደግፉ ኃይሎች መበራከት ተፅዕኖአቸው ከፍተኛ ነው የሚሉት፡፡ በተለይ ጽንፈኛና አክራሪ እስልምናን ለመሸከም ጀርባው የተመቸው ሻዕቢያ በ‹‹እኔ ከሞትኩ…›› ሥሌት ቀጣናውን ለማተራመስ ወደኋላ እንደማይል እየታመነ መጥቷል፡፡
ከእነዚህ መሬት ላይ ካሉ እውነታዎች አንፃር ይመስላል የኤርትራ መንግሥት በድፍረትና በይፋ የኢተዮጵያ መንግሥትን የሚፋለሙ ኃይሎችን እየደገፈ፣ እያሠለጠነና እያስታጠቀ ማሰማራቱን የገፋበት፡፡ ከዚህም በላይ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና ፕሮፓጋንዳ ጭምር ኢትዮጵያን የሚያዳክሙና አገር የሚበትኑ የዘረኝነትና የጥላቻ ቅስቀሳ ውስጥ የገባው፡፡ የዚህን ሥርዓት እኩይ ምግባር ደግሞ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ቅሬታ ያላቸው አገሮችም እንደሚደግፉት ከመጠርጠርም በላይ የሚታይ ሆኗል፡፡
በመሆኑም ወቅታዊው ቀጣናዊ ሁኔታ ብቻ ኢሕአዴግ መራሹ ሥርዓት ከተገዳዳሪዎቹም ጋር ሆነ ከሁሉም የአገሪቷ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሆደ ሰፊነት እንዲወያይ ያስገድደዋል፡፡ ዓይኑን ገልጦ ለተመለከተ የፖለቲካ ተንታኝም ሆነ ከግትርነት ወጥቶ ለአገሩ የሚያስብ መሪ መደራደርና ውይይትን እንደ ነውር ሊቆጥር አይገባም፡፡ ውይይት ጥቅምን ብቻ አያስጥልም፡፡ የሚያስገኘው የጋራ ፋይዳም አለ፡፡ ስለዚህ አገርን ከትርምስ ውስጥ ለማውጣት አማራጭ ሆኖ መታየት አለበት፡፡
ለማጠቃለል
አገራችን ምንም እንኳን በተስፋ ሰጪ መንገድ ላይ ብትሆንም፣ ጉዞዋ በመንታ መንገድ ላይ የሚገኝም ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ የውስጥ ፖለቲካም የቀድሞ ዓይነት ጥንካሬ የሌለውና ግራና ቀኝ የሚረግጥ መስሏል፡፡ በዚህ ላይ የሕዝቡ አለመርካትና ለውጥ መሻት፣ የፖለቲካ ኃይሉ በርዕዮተ ዓለም ቢስማማም ባይስማማም በጋራ መሠለፍ፣ እንዲሁም ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች መንግሥት ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ስለሆነም መፍትሔው ሁሉን አቀፍ ውይይት ነው የሚል እምነት የብዙዎች እየሆነ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Lzeru@yahoo.comማግኘት ይቻላል፡፡
