በጌታቸው አስፋው
የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የብሔራዊ ኢኮኖሚ አባት በሆነው ጆን ሜናርድ ኬንስ አነሳሽነትና ተሳትፎ በብሬተንውድስ ማሳቹሰትስ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1944 ሲቋቋሙ ዋናው ዓላማቸው የአገሮችን ገንዘብ ለማገበያየት፣ የምንዛሪን ዋጋ ለማመጣጠን፣ ምንዛሪ ለቸገራቸው አገሮች በቀላል የወለድ መጣኝ ለማበደር፣ መጠባበቂያ ለመያዝ፣ የገንዘዘብ ዕዳ ለማወራረድና በማዕከላዊነት ለመምራት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ይህነንኑ አገልግሎታቸውን ከመስጠታቸውም በተጨማሪ ለአገሮች ብድር ለማግኘትና የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ አገሮች ሄደው መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የእነርሱ ምስክርነት አስፈልጓል፡፡
ከእነዚህ ተቋማት ጋር ጥቅምና ጉዳትን መዝኖ ምንዛሪን በማርከስ አለመስማማት የሚቻል ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ህልውናቸው በብድርና በውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ላይ ለተመሠረተ አገሮች ምስክርነታቸውን ላለማጣትም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ኢኮኖሚስቶች ሀብትን አመጣጥኖ በማደላደል በግል ኢኮኖሚው የገበያ ውጤታማነት (Microeconomic Market Efficiency) አምነው የሚሟገቱና ለብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ (Microeconomic Policy) የቆሙ ተብለው ለሁለት ጎራ ሲከፈሉ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሁለቱን የግል ኢኮኖሚውን የገበያ ሕግጋትና የብሔራዊ ኢኮኖሚውን ፖሊሲ ማጣመር ይገባል የሚሉ የግል ኢኮኖሚው መሠረታውያን ለብሔራዊ ኢኮኖሚው (Microeconomic Foundations of the Microeconomic) የሚሉ ሦስተኛ ጎራ የየራሳቸውን አመለካከት የሚተነትኑበት ዘመን ላይ ነን፡፡
የእነዚህን የኢኮኖሚ አስተሳሰብና አመለካከት ጎራዎች አንድነትና ልዩነት የየአንዳንዳቸውን ጥቅምና ጉዳት ጠንቅቆ ማወቅ፣ የአገርን ኢኮኖሚ ለሚያስተዳድሩ መንግሥታት የኢኮኖሚ አማካሪ ባለሙያዎች ጉዳዩ የሕዝብ ጉሮሮ ስለሆነ ግዴታ እንጂ ውዴታ አይደለም፡፡
በተለይም በብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እናምናለን የሚሉ የመንግሥት ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካሪዎችና የብሔራዊ እቅድ ባለሙያዎች፣ ፖሊሲያቸውና ዕቅዳቸው ሀብትን በማደላደልና በምርታማነት ከግል ኢኮኖሚ የገበያ ሕግጋት ውጤታማነት መሻሉን በተግባር ማስመስከር አለባቸው፡፡ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የሚያጠነጥኑት በሁለት ዓይነት የፖሊሲ መሣሪያዎች በመንግሥት ገቢና ወጪ የበጀት ፖሊሲና በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ ላይ ነው፡፡
ለጊዜው በዚህ ጽሑፍ የምዳስሰው የጥሬገንዘብ ፖሊሲውን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የዓለም ባንክ ኃላፊዎች ከገንዘብ ሚኒስትሩና ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር በውጭ ምንዛሪ መጣኝ የብርን ዋጋ በማርከስ ሐሳብ ላይ ተከራከሩ የሚል ዘገባ በሪፖርተር ጋዜጣ ኅዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ዕትም ስላነበብኩ፣ ይህ ክርክር እንደ መነሻ ስለሆነኝ ነው፡፡
የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ
ባለፉት ሃያ ወራት ውስጥ በሪፖርተር ዕትሞች ባቀረብኩዋቸው አሥራ ሰባት ጽሑፎች በሁሉም ላይ ስለምርት ኢኮኖሚና ስለጥሬ ገንዘብ ኢኮኖሚ ተዛምዶ በቂ ትኩረት አለመስጠት፣ የማታ ማታ እንደሚጎዳን ጠንከር ያሉ አስተያየቶች ስሰጥ ቆይቼአለሁ፡፡
ሐሳቡ የእኔ ሳይሆን የታላላቅ ኢኮኖሚስቶች ምክር ነው፡፡ አስፋፊ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ (Expansionary Monetary Policy) በሕግ ገደብ (By the rule of the law) ካልተገደበ፣ በልክ ካልተመጠነና በዘፈቀደ (By Discreation) ካደገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርትን ቢያሳድግም፣ በረጅም ጊዜ ግን ውጤቱ ዋጋን ማናርና ጥሬ ገንዘቡን ዋጋ በማሳጣት የብራችንን የምንዛሪ መጣኝ ማርከስ ነው፡፡
በተለይም መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ዕትም የአደጋ ጠርዝ ላይ የጣሉን የኢኮኖሚ ጉዳዮች በሚል ርዕስ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን ሠንጠረዥን (Balance of Payment Table) በመተንተን ያለንበትን አስደንጋጭ ሁኔታ አሳይቼአለሁ፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የጥሬገንዘብ መሠረት ሆነው ተፅዕኖ በሚያሳድሩት በባንክ ሁለት የሀብት ዓይነቶች የውጭ ምንዛሪ ሀብትና የአገር ውስጥ ብድር ሀብት ንፅፅር ላይም ከድጡ ወደ ማጡ አካሄድ እያሳየ መሆኑን በአጭሩ ጠቅሼአለሁ፡፡ ከዚህ ቀጥዬም በመረጃዎቹ አማካይነት በተጨባጭ አመለክታለሁ፡፡
የጥሬገንዘብ አካል የባንክ ሀብቶች ንፅፅር
የበጀት ዓመት | የውጭ ምንዛሪ ሀብት በቢሊዮን ብር | የአገር ውስጥ ብድር ሀብት በቢሊዮን ብር | የውጭ ምንዛሪ ሀብት ከአገር ውስጥ ብድር ሀብት ንፅፅር |
2003 | 55.5 | 135.5 | 41% |
2004 | 39.8 | 189.1 | 21% |
2005 | 45.6 | 233.4 | 19.5% |
2006 | 56.1 | 299.7 | 18.7% |
2007 | 37.5 | 393.5 | 9.5% |
ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. የባንክ የውጭ ምንዛሪ ሀብት ከአገር ውስጥ ብድር ሀብት ጋር ሲነፃፀር፣ በ2003 ዓ.ም. ከነበረበት 41 በመቶ በየዓመቱ ቀንሶ በ2007 ዓ.ም. ዘጠኝ በመቶ ብቻ ሆኗል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ገና ባይወጣም ሦስት ቢሊዮን ዶላር ያልሞላው ኤክስፖርትና ሃያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሆነው የ2008 ዓ.ም. ኢምፖርት በሚያስከትለው የውጭ ንግድ ጉድለት የውጭ ምንዛሪ ሀብትን ስለሚቀንስ፣ በ2008 ዓ.ም. ንፅፅሩ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ ሀብትና የአገር ውስጥ ብድር ሀብት ንፅፅር ሁኔታ በብር የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የአገሪቱ ቁልል የውጭ ዕዳ ክምችትም (Outstanding Debt Stock) ይጨምራል፡፡
የብር ሸቀጦችን የመግዛት አቅም ጠንካራ እንዲሆንና በውጭ ምንዛሪ መጣኝ እንዳይረክስ ማድረግ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም ራሱ ለመንግስትና ለንግድ ባንኮች የሚሰጠውን ብድር ከመቆጣጠርም በላይ፣ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱትን የንግድ ባንኮችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ይገባዋል፡፡
ብዙ ሰዎች ስለ ጥሬ ገንዘብ ሲነገር በገበያ ውስጥ የሚዘዋወርን ጥሬ ብር ማለት ሊመስላቸው ይችላል ነገር ግን በንግድ ባንኮች ቆጣቢዎች የሚያስቀምጡት ተቀማጭ ወይም ንግድ ባንኮች በተቀማጩ ላይ ተመርኩዘው ተቀማጩን አርብተው በማበደር የሚፈጥሩት ብድርም ጥሬ ገንዘቦች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ለጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያደረገው በብሔራዊ ባንክ የቀረበው በገበያ ውስጥ የሚዘዋወረው ጥሬ ብር ይሁን፣ ወይም የንግድ ባንኮች ተቀማጭ በሚከተለው ሠንጠረዥ ተመልክቶ መረዳት ይቻላል፡፡
የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶች በቢሊዮን ብር
የበጀት ዓመት | በብሔራዊ ባንክ አቅራቢነት በገበያ ውስጥ የሚዘዋወር ጥሬ ብር | የንግድ ባንኮች ቀቀማጭ (ተንቀሳቃሽ፣ የቁጠባና የጊዜ ተቀማጮች) | ጠቅላላ ለገበያ የቀረበ ጥሬ ገንዘብ | የጥሬ ብርና የተቀማጭ ንፅፅር |
2003 | 32.6 | 112.8 | 145.4 | 29% |
2004 | 38.5 | 151.0 | 189.5 | 26% |
2005 | 45.7 | 189.6 | 235.3 | 24% |
2006 | 53.2 | 244.5 | 297.7 | 22% |
2007 | 60.5 | 310.7 | 371.2 | 20% |
አምናና ከዚያ በፊት በጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶች ነበሩ በተቋቋምኩ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከሺሕ ተነስቼ ሚሊዮኖች ውስጥ ገባሁ ይሉ የነበሩት፡፡ ከአምና ጀምሮ ግን ንግድ ባንኮች ሆነዋል በተቋቋምኩ በጥቂት ዓመታት ሚልዮኖችንና ቢልዮኖችን አተረፍኩ የሚሉት፡፡ ለቆጣቢው ከዋጋ ንረት በታች በሆነ የኪሳራ ወለድ መጣኝ (Negative Real Interest Rate) እየከፈሉ እነርሱ የቆጣቢውን ሦስት እጥፍ ወለድ የሞኖፖል ትርፍ ዝቀው ከቢሊዮን አልፈው ትሪሊየን ውስጥስ ቢገቡ፣ ማን ተቆጣጣሪ አላቸውና ነው በጥሬ ገንዘቡ እየከሰረ የተነገደበት ቆጣቢው ለእግዜር ሰጥቶ ዝም ብሏል፡፡
ጆንያ ለመቁጠር ሎንዶን ሄዶ መማር
ብዙ የቅርብ ጊዜ ኢኮኖሚስቶች ከአሜሪካ በተለይም ከቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ቢበቅሉም፣ የእንግሊዝ ሎንዶን አዳም ስሚዝ፣ ዴቪድ ሪካርዶና ሌሎች ጥንታውያን ኢኮኖሚስቶችና የብሔራዊ ኢኮኖሚ አባት የሆነው ኬንስ የበቀሉባት ዘመናዊ ኢኮኖሚክስ የተወለደባት አገር ናት፡፡ ብዙ የእኛ ምሁራንም ሄደው ተምረውባታል፡፡ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ እንደ እኛው ዋሸራ የቤተ ክህነት ትምህርት ቤት ከየትኛውም አገር በላይ በርካታ ምሁራን ያቀኑትም ወደ ሎንዶን ነበር፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በእስያ፣ በአፍሪካ ሄደው ብዙ ሰዎች ተምረዋል፡፡ አንዳንዶቹ አገር ቤት ተመልሰውም የፖሊሲ አማካሪ ሆነው ይሠራሉ፡፡ እነዚህ በአገር ውስጥና ኢኮኖሚክስ በተፈጠረባቸው አገሮች በሕዝብ ገንዘብ ተልከው የተማሩ የኢኮኖሚ አማካሪዎች፣ ስለብሔራዊ ኢኮኖሚያችን ስኬት ምን ይላሉ? የፖሊሲ ለውጥ የሰዎችን የወደፊት ግምት ቀይሮ የምርት፣ የሠራተኛ፣ የካፒታል፣ የሁሉንም ገበያዎች ማጣሪያ አጠቃላይ እኩልነት የኢኮኖሚ ልኬት ሞዴልን ውጤታማነት (Markets Clearing General Equilibrium Econometric Model Effectivenes) ያከሽፋል የሚሉ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቃዋሚና የግል ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተሟጋች ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች ሲናገሩ አንዳንድ ሰዎችን ሁሌም ማታለል ይቻላል፣ ሁሉንም ሰዎችም አንዳንድ ጊዜ ማታለል ይቻላል፣ ሁሉንም ሰዎች ሁሌም ማታለል ግን አይቻልም የሚል የአብረሃም ሊንከንን ንግግር ጠቅሰው፣ በሒሳብ ሥሌት ላይ በተመሠረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ይገልጻሉ፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የምርት ገበያውም፣ የሠራተኛ ገበያውም፣ የካፒታል ገበያውም የመሬት ገበያውም ተዛብተዋል፡፡ መዛባታቸውንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ አውቋል፡፡ የምርት ገበያው ዋጋ ሰው አስመርሯል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ሥራ አጥቷል፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት የምንዛሪ መጣኙን አዛብቶታል፡፡ በዓለም ታላላቅ ከተሞች እንኳ ባልታየ ዓይነት በአዲስ አበባ የአንድ ካሬ ሜትር መሬት ዋጋ ሦስት መቶ ሃምሳ አምስት ሺሒ ብር ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ድምፅ ሁላችንንም ሁሌም ማታለል አይቻልም ብሏል፡፡
በጊነስ ቡክ ሊመዘገብና ሊቃውንትን ለምርምር ሊጋብዝ የሚችለው በጆንያ ተለክቶ በጥሬ ገንዘብ ስታቲስቲክስ መረጃ መልክ ተተምኖ የቀረበው በ1983 ዓ.ም. አሥር ቢሊዮን ብር ገደማ የነበረው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት፣ በ2008 ዓ.ም. አንድ መቶ ሃምሳ እጥፍ አድጎ አንድ ተኩል ትሪሊየን መድረሱ ከገበያው ፍላጎትና አቅርቦት መጣጣም መረጃ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ የሕዝብ ዓመኔታን አጥቷል
የወጣቱ ሥራ አጥነት ለአገር ህልውና የሚያሠጋ ሁከት ከመቀስቀሱም በላይ፣ የከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ገና መቋጫ ብልኃትም አልተገኘለትም፡፡ በውጭ ምንዛሪና በካፒታል እጥረት ምክንያት ብዙ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች ተጓትተዋል፡፡ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የከተማና የገጠር መሬት ሽሚያው ሕዝብን ከሕዝብ ከማጋጨቱም በላይ ለፀጥታ አስከባሪዎችም ፈታኝ ጊዜ ሆኖ ከርሟል፡፡
እህል በጆንያ እየለኩ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮችም ነፍሶባቸዋል፡፡ ብሪክስ የተባሉትና በቅርቡ በፍጥነት ስለማደጋቸው የተመሰከረላቸው በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካም አርጅተዋል፡፡ አሁን ዓለም እያወራ ያለው ስለእኛ ዕድገት ነው ብለው እስከ አሥራ አንደኛው ሰዓት ያወሩ የነበሩ የኢኮኖሚያችን ባለሙያዎች በአሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ የዋጋ ንረቱን አምነው እንቀንሰዋለን አሉ፡፡ ሁከት የቀሰቀሰው የወጣቱ ሥራ አጥነት ነው አሉ ለዓለም ባንክ ባለሙያዎቹ ምላሽ ሲሰጡ፡፡ ከጆንያ ምርት ውጪ ምንም ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ሸቀጥ ስለሌለን የብር ምንዛሪ አናረክስም አሉ፡፡
የጆንያ ምርት ቆጠራ በደጉም ጊዜ በክፉም ጊዜ አይቀርም፡፡ የዓለም መገናኛ ብዙኃን በዕለት ተዕለት የቢዝነስ ዘገባቸው ኢኮኖሚያቸውን በገንዘብ ገበያ መጣኞች፣ በቦንድና በአክሲዮን ዋጋዎች መውጣትና መውረድና የወለድ መጣኞች መውደቅና መነሳት አመልካች (Index) ይለካሉ፡፡ የእኛ መገናኛ ብዙኃንም በመሳለሚያ ገበያ የኩንታል ጤፍ ዋጋ፣ በአትክልት ተራ የኩንታል ድንች ዋጋ የቢዝነስ ዘገባ ያቀርቡልናል፡፡
በዚህ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በሌሎች አገሮች የገንዘብ ገበያ መጣኞች የምርት ኢኮኖሚ መለኪያዎቸ ነፀብራቆች ናቸው፡፡ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ጥቅል መረጃ ደረጃ በጆንያና በካርቶን መለካት ቀርቷል፡፡ እኛ ኢኮኖሚያችን ማደጉን ለመናገርም ሆነ የቢዝነስ ዘገባ ለማቅረብ፣ በዓለም ገበያ ለመወዳደር አለመቻላችንን ለመግለጽም መለኪያችን ጆንያ ነው፡፡ ራሳችንን በጆንያ ቆጠራ ልክ ገድበን ካሳነስነው ሁሌም ጆንያ ቆጣሪ ነው የምንሆነው፡፡
የአሥራ አንደኛው ሰዓት ንሰሐ
በጆንያ ከሚለካ የግብርና ምርት በስተቀር ምንም ሌላ የኤክስፖርት ምርት የሌለን ሰዎች፣ ከውጭ የሚገባውን ሸቀጥም በአገር ውስጥ ምርት መተካት የማንችል ሰዎች፣ የብርን ዋጋ አርክሰን ምን እንጠቀማለን ማለታቸውን እኔም የምጋራው ነው፡፡ ቢሆንም በሌላ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ የብራችን ምንዛሪ መጣኝ እንዲስተካከል ማድረግ የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው፡፡ ቀድሞውንም ለዚህ ያበቃን የብሔራዊ ባንክ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ መሆኑም አይዘነጋም፡፡
ጥሬ ገንዘብ የተፈጠረው የምርት ኢኮኖሚውን ለማገበያየትና ለመለካት እስከሆነ ድረስ የምርት ዋጋ አመልካች ከመሆን አልፎ የራሱ ዋጋ የለውም፡፡ የጥሬ ገንዘብ ዋጋ የሚተመነው ሊገዛ በሚችለው ምርት መጠን ነው፡፡ ስለዚህም ምርቱ ሳይኖር ጥሬ ገንዘቡን ማብዛት የምርቱን ዋጋ መጣል ነው፡፡ ለዚህም ነው በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ የውጭ ሸቀጥ ለመግዛት ከሚያስችለው የውጭ ምንዛሪ በቀር የአገር ውስጥ ጥሬ ገንዘብ ለአገር ሀብትን ይለካል እንጂ ሀብት አይደለም የሚባለው፡፡
የአገር ውስጥ ምንዛሪ (Currency) ከሌላ አገር ምንዛሪ ጋር በመገበያያ ዋጋ የሚለካው በእርግጠኛ መመነዛዘሪያ መጣኝ (Effective Real Exchange Rate) የአንድ አገር ምንዛሪ ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ ከሌላ ተገበያይ አገር ምንዛሪ ሸቀጦችን በመግዛት አቅም ጋር ሲወዳደር፣ ወይም ከጊዜ ወደ ጊዜ በተመናዛሪዎቹ አገሮች ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት ልዩነት ከግምት ባስገባ የመመነዛዘሪያ መጣኝ ነው፡፡
ስለዚህም ለዛሬው የምንዛሪያችሁን ዋጋ ቀንሱ ምክንያት የሆነው ባለፉት ዓመታት ብራችን በአገር ውስጥ ሸቀጥን የመግዛት አቅሙ በመዳከሙ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ከልኩ በማለፉ ነው፡፡
ያለፉት ዓመታት የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ዕድገት
የበጀት ዓመት |
መጠን |
የመጠን ልዩነት |
ዕድገት | የአምስት ዓመት ዕድገት አማካይ |
2002 | 104 |
|
|
29% |
2003 | 145 | 41 | 39% | |
2004 | 189 | 44 | 30% | |
2005 | 235 | 46 | 24% | |
2006 | 298 | 63 | 27% | |
2007 | 371 | 73 | 25% |
የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱ ዕድገት መጣኝ እየቀነሰ ቢመጣም በአካፋዩ መነሻ መተለቅ ምክንያት እንጂ፣ የአቅርቦቱ መጠን እየጨመረ እንደመጣ እናያለን፡፡ የእርግጠኛ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዕድገትን በየዓመቱ 11 በመቶ ይሁን ብለን ተቀብለን እንኳ፣ ከአምስቱ ዓመት አማካይ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ዕድገት 29 በመቶ ውስጥ 11 በመቶው ለምርት ዕድገት ዋለ ብንል ቀሪው 18 በመቶ የዋለው ለዋጋ ንረት ነው፡፡
ከጥሬ ገንዘብ ትንታኔ ፈቀቅ ብለን በአጠቃላይ ስለምርት ኢኮኖሚና ስለገንዘብ ኢኮኖሚ ብናስብ፣ እኛና ሌሎች አገሮች ያሉበትን ሁኔታ ስናነፃፅር እኛ በአሞሌ ጨው ዘመን እንደምንገኝ እንገነዘባለን፡፡ ሃያን አሥራ አሥር፣ ሰላሳን ሃያ አስር፣ አርባን ሰላሳ አሥር፣ ወዘተ ብለው ይቆጥሩ የነበሩት አያት ቅድመ አያቶቻችን ከእነርሱ ያለፈ የገንዘብ ቋንቋ እንደሌለን ቢያውቁ፣ እዚያው ባስቀመጥናቸው ቦታ እንደተቀመጡ ናቸው ይሉን ነበር፡፡
በዚህ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርትን በጆንያ እየቆጠሩና በአሞሌ ጨው ጥሬ ገንዘብ እየለኩ ኢኮኖሚን መምራት አልቻል ብሎ፣ በአሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ በቀውሱ አናዛዥ የንሰሐ አባትነት ምሎ ተገዝቶ እውነቱን መናገሪያ ጊዜ ላይ አድርሶናል፡፡ የንሰሐ ጊዜ ሆኖ ብዙ አናዞናል፡፡
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሚናገሩት ንግግር ውስጥ አንድ አስገራሚ አባባል አለ፡፡ አሜሪካ ሌሎችን ከምትመክርበት የዓለም አንድ የገበያ መንደርነት የግሎባላይዜሽን ሥርዓት ቢያፈነግጥም፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው ‹‹የአሜሪካንን ምርት ግዙ፣ አሜሪካውያንን ቅጠሩ፣ አሜሪካውያንን መቅጠር ራስን መቅጠር ነው›› የሚል እንደሚሆን ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ እንደሳቸው የአገርን ምርት መግዛት ማለት የአገርን ሰው መቅጠር ነው፡፡
በዓለም ገበያ ተወዳድራ የማሸነፍ ዕድል ላላት ታላቅ አገር የአገራችሁን ግዙ፣ የአገራችሁን ሰው ቅጠሩ፣ የአገርን ሰው መቅጠር ራስን መቅጠር ነው ሲሉ፣ በዓለም ገበያ ለመወዳደር ዕድሉ የሌላት ለማደግ የምትፈልግ አገር ምን ዓይነት የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነትና የውጭ ንግድ ፖሊሲ ሊኖራት ይገባል?
የእኛ አስፋፊ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ለእኛ የሆነው “የቻይናን ግዙ፣ ቻይናውያንን ቅጠሩ” ነው፡፡ ወርቅ ሽጦ ጥብቆ ከውጭ መግዛት፣ እህል ሽጦ የቤት ቁሳቁስ ከውጭ መግዛት፣ የቁም እንስሳትን ሽጦ መጫወቻ አሻንጉሊት ከውጭ መግዛት ለራስ ሳይሆን ለሌላ አገር ዜጋ የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡ ሥራውንና የሠራተኛ ገበያውን ወደ ውጭ አውጥቶ ሽጦ፣ ወጣቶችን ሥራ ፍጠሩ እያሉ መጨቅጨቅስ ምን ፋይዳ አለው?
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡
